አቶ ገዱ ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስትር ጋር የስልክ ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአየርላንድ የውጭና ንግድ ሚኒስትር ሳይመን ኮቪኒይ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ የሁለቱን ሃገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።
አቶ ገዱ ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደምትሰራ ጠቅሰው፥ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ከአየርላንድ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ወረርሽኙን ለመግታት የሁሉም አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ገዱ፥ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየወሰደች ያለውን እርምጀ እና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን ለመግታት እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ የሚያወጣቸውን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
የአየርላንድ የውጭና ንግድ ሚኒስትር ሳይመን ኮቪኒይ በበኩላቸው አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ደስተኛ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጠናው ያላትን ሚና ያደነቁት ሚኒስትሩ በአትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመግታተ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አበረታች እንደሆኑ መገንዘባቸውን ጠቁመዋል።
አየርላንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሰራለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዓለም የጤና ድርጅት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑንና ሁሉም አካል ሊደግፈው ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።