የሚሳኤል ክፍሎችን በድብቅ ለአሜሪካ የላከው ሩሲያዊ የ12 ዓመት ከ6 ወር እስራት ተፈረደበት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የደህንነት ሰዎች ትዕዛዝ የሩሲያ ሚሳዔል ክፍሎችን በድብቅ ወደ አሜሪካ የላከው ግለሰብ በ12 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የሩሲያ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ፌዴራል ደህንነት አግልግሎት እንዳስታወቀው÷ ሰርጌይ ካባኖቭ የተባለው ግለሰብ ከአሜሪካ ደህንነቶች ተልዕኮ በመቀበል የሚሳኤል ክፍሎችን በላቲቪያ በኩል በድብቅ ወደ አሜሪካ ልኳል ብሏል፡፡
ግለሰቡ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የላካቸው የሚሳኤል ክፍሎች በሩሲያ የአየር ሀይል እና በራዳር ተኮር የጦር መሳሪያዎች ውስጥ የሚያገለግሉ የሚሳኤል ክፍሎች መሆናቸውም ነው የተገለፀው፡፡
ግለሰቡ የሚሳኤል ክፍሎቹን ለአሜሪካ የደህንነት ሰዎች በእንጨት ሳጥን ውስጥ በማድረግ ለማስረክብ ሲሞክር የሩሲያ ብሔራዊ ደህንነት ሰራተኞች ባደረጉት ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል፡፡
ግለሰቡ በቴቨር ከተማ ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ከተባለ በኋላ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት የሩሲያ እስር ቤት ቅጣቱን ይጨርሳል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡