ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍላጎት የሚያስተናግድ እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው -አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የቡድን 77 እና ቻይና የመሪዎችና የመንግስታት ጉባኤ በኩባ ሀቫና ከተማ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በተናጠል የሚጣሉ ማዕቀቦችና ኃይልን መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ እርምጃዎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ልማት ለውጦችን ያስተጓጉላሉ ብለዋል።
በደቡብ-ደቡብ የትብብር መድረክ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ ፈጠራን ለማሳደግና ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ወሳኝ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እየተገበረች ባለው የዲጂታል ስትራቴጂ ሰፊውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር ራዕይ ሰንቃ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ስትራቴጂውን በመተግበር አበረታች ውጤቶችን እያገኘች መሆኑን አቶ ደመቀ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የቡድን 77 እና ቻይና የመሪዎችና የመንግስታት ጉባኤ በዛሬ ውሎው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳቦችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።