የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ የቱርክ መርከቦች ሊቢያ ደረሱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሊቢያ የጎርፍ አደጋ ተጎጂዎች የሚሆን ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ሁለት የቱርክ የባህር ሃይል መርከቦች ሊቢያ ደርሰዋል።
መርከቦቹ 360 ድጋፍ ሰጪ ሰዎች እና 122 ተሽከርካሪዎች መያዛቸው ተገልጿል።
የቱርክ ብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ድጋፍ ለመስጠት ከቱርክ የተንቀሳቀሱ መርከቦች ሊቢያ ደርሰዋል።
ድጋፉን ለመስጠት ከተጓዙት ውስጥ የቱርክ የአደጋና አስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ሃላፊዎችን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች የሚፈለገውን ድጋፍ መስጠት የሚችሉ ሰዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
አምቡላንስን ጨምሮ 122 መኪናዎች የድጋፍ አሰጣጡን ለማገዝ መላካቸው ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሶስት የመስክ ሆስፒታል በማቋቋም የድጋፍ ስራው የሚከናወን ሲሆን ምግብ፣ መጠለያና መድሃኒት በመስጠት የህይወት አድን ስራ እንደሚሰራ የአናዶሉ ዘገባ አመልክቷል።
ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን የሚያደርስ ተጨማሪ መርከብ ወደ ስፍራው ለመላክ የሚያስችል ዝግጅትም መደረጉን ተጠቁሟል።