Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ዘመን መለወጫ በቤት ታስቦ ይውላል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፊቼ ጫምባላላ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በአደባባይ እንዳይከበር የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች ወሰኑ።

የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በወቅቱ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ከግምት በማስገባት በቤት ታስቦ እንደሚዋል ነው የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎችና አያንቶዎች የተገለፁት።

የዘመን መለወጫ በዓሉ በቀጣዩ ሳምንት ግንቦት 12 እና 13 እንደሚውል የብሄሩ አያንቶዎች ጠቁመዋል።

ፊቼ ጨምበላላ የሀገር መሪ እና ታላላቅ የሃገር ሽማግሌዎች ቢሞቱ እንዲሁም ሀገራዊ ችግሮች ሲከሰቱ በበዓሉ ጉዳይ በመመካከር እንደሚሸጋግር ሽማግሌዎቹ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት የዘንድሮው የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ በዓል ካለምንም ዝግጅት እና ቄጣላ እንዲያልፍ ወስነዋል።

እለቱን እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ ያገኘውን እየቀመሰ ከልጆቹ ጋር እንዲያሳልፉ ወስነዋል።

ከዚህ ቀደም የሚከወኑ የባህሉ ትውፊቶች ተገድበዋል ያሉት የሀገር ሽማግሌዎቹ፥ በየወረዳውም ሆነ በየጉዱማሌው ምንም አይነት ዝግጅት እንዳይኖርም አሳስበዋል።

የፈንጣጣ ወርሽኝ በተከሰተበት ወቅት እንደዚሁ በዓሉ መተላለፉን አውስተው ኮሮና ቫይረስን ከሀገራችን ለማጥፋት ራሳችንንና ወገኖቻችንን ልንጠብቅ ይገባልም ብለዋል።

የሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ወቅቱ አስቸጋሪ በመሆኑ ወጣቶች የአባቶችን ምክር ሰምተው ጤንነታቸው የተጠበቀ ሆኖ በቀጣይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያሳልፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደዚህ አይነት ኩነቶች ሲከሰቱ አያንቶዎች ቀድሞውኑ የራሳቸው ባህላዊ ህግ ስላላቸው ካለምንም ቅድመ ዝግጅት ከግንቦት 12 እና 13 እያንዳንዱ በየቤቱ ካለምንም ንኪኪ ሊያከብር ይገባል ብለዋል።

የባህሉን እሴት በየሚዲያው እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

በዓሉ ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን ፈውስ እንዲያወርድ ተመኝተዋል።

በያሬድ ጌታቸው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.