Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለስድስት ወራት ከቆየ ኢትዮጵያ 139 ቢሊዮን ብር የሚገመት ምርት ልታጣ ትችላለች- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሺኝ ለስድስት ወራት ከቆየ ኢትዮጵያ 139 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የምርት መቀነስ ወይም የምርት እጦት ሊያጋጥማት እንደሚችል በወረርሺኙ ምጣኔ ኃብታዊ ተጽዕኖ ላይ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባበሪነት የሚካሄደው ሳምንታዊውና አምስተኛው በኮቪድ-19 ላይ ያተኮረው ውይይት ተካሂዷል።

በዛሬው መርሃ ግብርም በርከት ያሉ ምሁራን ወረርሽኙ በአገሪቷ ላይ እያስከተለ ስላለው ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር አስተባበሪነት ወረርሽኙ በአገሪቷ ምጣኔ ኃብት ሊያስከትል የሚችለው ተጽዕኖን የተመለከተው ጥናት ቀርቧል።

ጥናቱን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ታደለ ፈረደ ”ችግሩ የዓለምን ኢኮኖሚ እርቃኑን ያስቀረ ክስተት ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያም በአቅርቦት ችግር፣ በፍላጎት መጨመርና አጠቃላይ የፋይናንስ ሂደት ላይ አደጋ መደቀኑን ገልጸዋል።

በዚህም ቀድሞውኑ በርካታ ችግር ያለባት ኢትዮጵያ የቱሪዝምና የመስተንግዶ ዘርፉ፣ ግብርናው፣ አምራች አንዱስትሪውና የውጪ ንግዱ ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑን ጥናቱን አጣቅሰው ያብራራሉ።

”ወረርሽኙ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ አገሪቷ 139 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ምርት የመቀነስ ሁታ ያጋጥማታል” ብለዋል።

ጉዳት የሚያስከትሉ ነገሮችን ለይቶ የቅደመ መከላከል ስራ መስራት በተለይም በጤናው ዘርፍ በቀጣይ ሊደረጉ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ነው ይላሉ ዶክተር ታደለ ጥናቱን መነሻ አድርገው።

በተጨማሪም አስቀድሞም እየተተገበረ የሚገኘውን የ’ሴፍቲ ኔት’ መርሃ ግብር በከተማም በገጠርም ማስፋት፣ የተቋረጡ የመሰረታዊ ፍጆታ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን መልሶ ማጠናከርም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህ ደግሞ ጠቃሚው የግል ነጋዴዎች ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን የሕብረት ስራ ማሕበራትን ማጠናከርና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማጠናከርና መደገፍም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የወረርሽኙ ማህበራዊ ተጽዕኖዎችን በማስመልከት የውይይት መነሻ ንግግር ያደረጉት ዶክተር የራስወርቅ አድማሴም ”የመረጃ ስርጭቶች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሕዝቡ አወናባጅና አሳሳች መረጃዎች እንዳይደርሱት ማድረግ እንዲሁም እንደየ አካባቢውና እንደየ እውቀት ደረጃ መረጃ ማሰራጨት ማሕበረሰቡን ለመታደግ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

ዶክተር የራስወርቅ በተለያዩ አገሮች የተሰሩትን ጥናቶች ጠቅሰው ”ወረርሽኙ በአንዳንድ ሁኔታዎች ባልና ሚስት እንዲጨቃጨቁና የቤት ውስጥ ጥቃቶች እንዲባባሱ አድርጓል” ብለዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ሰዎች ቤት በሚውሉበት ጊዜ ከዚህ በፊት አግኝተው የማያውቁትን ቤተሰባዊ ጊዜ አግኝተው ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ በጎ ዕድል መፍጠሩንም አውስተዋል።

ምሁሩ እስካሁን በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ ‘ለስላሳ’ የመከላከል እርምጃዎች በበጎ ጎኑ የሚታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም አሁንም የገበያ ስፍራዎችን ጨምሮ ሌሎች ማህበረሰቡ የሚሰበሰብበት ቦታዎች ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ ሊተኮር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንዳልካቸው ስሜ ”ኢትዮጵያ በኢኮኖሚም በጤናም በኩል እኩል ጫና ተጋርጦባታል” ይላሉ።

እስካሁንም የአቅርቦትና ፍላጎት ችግሮች ማጋጣመቸውንና የሕዝብ ስነልቦና ጉዳት እንዳጋጣመ አብራርተዋል።

”በተለይም በኢትዮጵያ ከተሞች ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው በላይ በራሱ መንገድ ስራ ውስጥ ገብቶ መተዳደሪያ አድርጎት ኑሮውን እንደሚመራ ጥናት ያመለክታል” ብለዋል።

ከነዚህ ውስጥ እስከ 800 ሺህ የሚደርሱ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ቀጥታ ተጎጂ የሚሆኑ ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ ለችግር ተጋላጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ወረርሽኙ ከምንም በላይ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ክፉኛ እየጎዳ መሆኑን ተናግረው፤ የአገር ውስጥ ምርት እድገቱም በሶስት ወር ውስጥ ከ9 በመቶ እስከ 3 ነጥብ 8 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል።

መንግስትም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኘውን የአስር ዓመት መሪ ዕቅዱን ለመከለስ መገደዱን አስታውሰዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማሪያም በበኩላቸው ”የከፋ ተጽዕኖ አገር ላይ እንዳይደርስ የምርምር ስራዎች ይከናወናሉ” ብለዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስካሁንም በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ ለመንግስት ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሃሳቦች መገኘታቸውን ሚኒስትሯ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.