Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ የህንጻ አዋጅ መስፈርቶችን በማይከተሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ የህንጻ አዋጅ መስፈርቶችን በማይከተሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች በሚሳተፉ አልሚ፣ ተቋራጭና አማካሪው ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት÷ በመዲናዋ ጥራታቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ የህንጻ ግንባታዎች እንዲከናወኑ እስከ ወረዳ ድረስ የተቀናጀ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተከናውኗል።

በዚህም የህንጻ አዋጅ መስፈርቶችን በማያሟሉ ፕሮጀክቶች ላይ በሚደረግ ቁጥጥር የሚወሰደው እርምጃ በአልሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በተቋራጩና አማካሪው ላይ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

በ2015 ዓ.ም የህንጻ አዋጁን የተላለፉ በተለይም በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች በግንባታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የተወሰኑ አካላት የግንባታ ሰራተኞችን እንዲሁም ማህበረሰቡን ለጉዳትና ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ግንባታ ማከናወናቸውን ተከትሎ በርካታ አልሚዎች ላይ ቅጣት መጣሉን አስታውሰዋል።

ከተጣለው ቅጣት ውስጥ 67 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ወደ 20 የሚጠጉ ፕሮጀክቶች እንደነበሩም ተናግረዋል።

  1. ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአያት ሪል እስቴት 8 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበት እንደነበር ጠቅሰው፥ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው አልሚዎች የህንጻ ግንባታ ፍቃዳቸው እንዲታገድ መደረጉንም አንስተዋል።

በተያዘው 2016 ዓ.ም ተቋሙ የነበረውን የሰው ኃይል ክፍተት በመቅረፍ እስከ ወረዳ ድረስ በተዋረድና በተቀናጀ መልኩ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የህንጻ አዋጁን የተለያዩ መስፈርቶችን በማያሟሉ አልሚ፣ ተቋራጭና አማካሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በጅምር የህንጻ ግንባታ ስራ ላይ የሚሰማሩ አካላት የሰራተኞቻቸውን የደህንነት ግብዓቶች እና ሌሎች መስፈርቶች እንዲያሟሉ አስቀድመው የግንዛቤ ስራ እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።

ማህበረሰቡም መንገድ በመዝጋት ጥንቃቄ የጎደላቸው ግንባታዎችን በሚያከናውኑ አካላት ላይ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.