Fana: At a Speed of Life!

የልብ ህመምን መከላከል ይቻላል?

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የልብ ህመም የልብን ስራ የሚያስተጓጉሉ የተለያዩ የልብና የደም ዝውውር ችግሮችን የሚያጠቃልልና ከባድ ከሚባሉት የህመም አይነቶች የሚመደብ ነው።

ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ሁሉንም ለሚያጠቃው የልብ ህመም ተጋላጭ ላለመሆን ጤናማ የኑሮ ዘይቤ መከተል ያስፈልጋል።

የልብ ህመም ምልክቶች የተለያዩ ቢሆኑም በአብዛኛው የልብ ህመም ምልክቶች የደረት ህመም፣ የጀርባና የአንገት ህመም፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ ምቾት ማጣት፣ መፍዘዝ፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የጨጓራ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ቃር፣ ማስታወክ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህ የልብ ህመም ምልክቶች በአብዛኛው የልብ ታማሚ ላይ የሚከሰቱ ቢሆንም በሴቶች ላይ የሚከሰተው የልብ ህመም ምልክት በወንዶች የልብ ህሙማን ላይ ከሚታየው የህመም ምልክት ሊለያይ እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ከዋና ዋናዎቹ የልብ ህመም መንስኤዎች መካከል የስኳር በሽታ፣ የተለያዩ የልብ እክሎች፣ የደም ግፊትና የደም ቧንቧ ችግር ይጠቀሳሉ፡፡

የልብ ህመምን የሚያባብሱ ችግሮች ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸውና ከቁጥጥራችን ውጪ የሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ከነዚህም ውስጥ ሲጋራ ማጨስ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ያለማድረግ፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብ የሚሉት ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው አባባሽ ሁኔታዎች ሲሆኑ በዘር፣ በጾታና በእድሜ ምክንያት የሚመጣን የልብ ህመም ግን መቆጣጠር የምንችለው አይደለም፡፡

በዘር የሚመጣን የልብ ህመም መከላከል ባንችልም ሌሎችን አይነቶች የልብ ህመም አይነቶችን ግን ጤናማ አመጋገብ በመመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ሲጋራ ባለማጨስና ሌሎች አባባሽ ሁኔታዎችን በመተው መከላከል እንችላለን ፡፡

አንድ ሰው የልብ ታማሚ መሆን ያለመሆኑን ከበሽታው ምልክቶች በተጨማሪ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ በሚደረግ ምርመራ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አንድ የልብ ታማሚ እንደ ልብ ህመሙ አይነትና የህመሙ ደረጃ በህክምና ሊረዳበት የሚችልበት አማራጭ ያለ ሲሆን ህክምናውም ቀዶ ጥገና በማድረግ፣ መድሃኒት በመውሰድና በሌሎች አማራጮች ሊከወን ይችላል፡፡

ምንጭ፦ ሄልዝ ላይን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.