Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ኩባን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ኩባን ጠንካራ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም በኩባ ሀቫና በተካሄደው የቡድን 77 እና ቻይና ጉባዔ ላይ በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ተሳትፏል።

አቶ ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኩባ ፕሬዚዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ እና ከሌሎች የሀገሪቷ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ ትብብር ከመደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በደምና በመስዋዕትነት ጭምር ልዩ ታሪከዊ ግንኙነት ያለው መሆኑን አቶደመቀ ገልጸዋል።

ሀገራቱ በትምህርት ዘርፍና ሌሎችም መስኮች ጠንካራ ትብብር ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው÷ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውም ጥልቅ ቁርኝት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ከኩባ ፕሬዚዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ ጋር በተደረገው ውይይትም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ጠንካራ ወዳጅነትና የትበብር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በሚኒስትሮች ደረጃ የምክክር መድረክ ለማካሄድ መስማማታቸውን ነው የገለጹት።

የኩባ ፕሬዚዳንት በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ የስራ ጉብኝት እንዲደረግ ግብዣ ማቅረባቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኩባ በተለያዩ መስኮች ይበልጥ በመተባበር የመስራትና የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልምዷን እንዳካፈለች መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አቶ ደመቀ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከጃማይካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሚና ጆንሰን ስሚዝና ከተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር ምክክር አድርገዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.