Fana: At a Speed of Life!

የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር ቴክኖሎጂን ማዳበርና መሳሪያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል – ዶ/ር ሊያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ ለበርካታ ሰዎች በተለይም ለህፃናት ሞት አይነተኛ ምክንያት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

ዘጠነኛው የፓን አፍሪካ የወባ ትንኝ መከላከል ማህበር ዓመታዊ ስብሰባና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየውን ስብሰባና ኤግዚቢሽን በማስመለክት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአፍሪካ የወባና ተዛማች በሽታዎች ስርጭት የህብረተሰብ ጤና ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በአህጉሪቱ የወባ ወረርሽኝ ለበርካታ ሰዎችና በተለይም ለህፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የወባ ወረርሽኝን መከላከል የሚቻል ቢሆንም በአፍሪካ አይነተኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ወረርሽኙ በተለይም በአምራቹ ሃይል ላይ ፈተና ቢሆንም በመከላከል ሂደት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የወባ በሽታን በመከላከል ባደረገው የተሳካ ጥረት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2021 ወባን በመቆጣጠር መሰረታዊ ለውጥ በማስመዝገብ በብሔራዊ ስትራቴጂው ከመቆጣጠር ወደ ማጥፋት ማሳደጓን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በ2017 ገቢራዊ በተደረገው ወባን የማጥፋት ስትራቴጂ በመጀመሪያው ዙር በ239 እንዲሁም በ2021 በሁለተኛው ዙር 565 ጣቢያዎች ማስፋፋት ተችሏል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ወባና ተዛማጅ በሽታዎችን በመቆጣጠር ተጨባጭ ለውጥ ቢመዘገብም በግጭትና መፈናቀል፤ በጎርፍና ድርቅ እንዲሁም የትንኞች መድሀኒትን መቋቋም ስርጭቱን እንዲያገረሽ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የወባ ስርጭትን በመቆጣጠር፣ ቴክኖሎጂዎችን በማዳበርና መሳሪያዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ስርጭቱን መግታት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የተከሰቱ አዳዲስ በሽታ አስተላላፊዎችን በመቆጣጠር በሽታውን ለማጥፋት ኢትዮጵያ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ መቀየሷንም ጠቅሰዋል።

ለዚህም ስኬት የዘርፉ ባለሙያዎችና የድጋፍ አጋሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፓን አፍሪካ የወባ ትንኝ መቆጣጠር ማህበር በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው በበኩላቸው÷ በአፍሪካ የወባ ትንኝን በመከላከል ወባን የማጥፋት ስትራቴጂ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙዎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ ደንጌ ያሉ በሽታዎችና አዳዲስ የወባ አስተላላፊ ትንኞች አማካኝነት ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅትም ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዘ ድጋፍ ያደርጋልም ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.