ሕገ-ወጥ የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ 11 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሕግ ውጪ ለስድስት ግለሰቦች የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ 11 ተጠርጣሪዎች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበ።
ክሱ የቀረበው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ተረኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾች 1ኛ በሌላ ወንጀል ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ከተማ ይዞታ አስተዳደር የሕግ እና የሰነድ ጉዳዮች አጣሪ ሽብሬ ንጉሴ ገ/ህይወት ፣ 2ኛ በንፋስ ስልክላፍቶ ክ/ከተማ ይዞታ አስተዳደር የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ውብአለም ሃይሉ ፣ 3ኛ በንፋስ ስልክላፍቶ ክ/ከተማ ይዞታ አስተዳደር የካርታ አፅዳቂ ባለሙያ ፀጋ አበራ እና የልደታ ክ/ከተማ የይዞታ ማህደር ባለሙያ መስከረም የሻው እንዲሁም 7 በግል ስራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ናቸው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት ክሶችን አቅርቧል።
በ1ኛው ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ከሌሎቹ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የልማት ተነሺ ሳይሆኑ ከ4ኛ እስከ 10ኛ ከተጠቀሱት ተከሳሾች በሀሰት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ክልል ውስጥ የቀርሳ ኮንቶማ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ከክፍለ ከተማው መሬት ልማት አስተዳደር ፅ/ቤት ዕውቅና ውጭ በአየር ላይ ማህደር እንዲደራጅ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም ለእያንዳንዳቸው ስፋቱ 500 ካሬ ሜትር የሆነ የመንግስት ቦታ በምትክነት በነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም በ6 ካርታዎች ላይ ክፍለ ከተማው የማያውቀውን ሀሰተኛ የሆነ የመዝገብ ቁጥር፣ የካርታ እና የቤዝ ማፕ ቁጥር በመሙላት ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አዘጋጅተው ካርታዎቹ ላይ በጋራ ፈርመው መስጠታቸው ተጠቅሷል።
ተከሳሾቹ አጠቃላይ ስፍቱ 3 ሺህ ካሬ ሜትር የመንግስት ይዞታ ላይ ወደ ሀሰት በተለወጠ የካርታ መብት የፈጠሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
ከ4ኛ እስከ 9ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች ደግሞ የልማት ተነሺ ሳይሆኑ ራሳቸውን የልማት ተነሺ እንደሆኑ አድርገው ሀሰተኛ ማህደር እና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በስማቸው እንዲዘጋጅላቸው ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ያገኙትን ሀሰተኛ ካርታ በሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ቀርበው ለ10ኛ ተከሳሽ መሸጥ መለወጥ እንዲችል መሉ ውክልና መስጠታቸውን እና ለዚህ ሕገ-ወጥ ተግባራቸው ከ10ኛ ተከሳሽ እያንዳንዳቸው 130 ሺህ ብር በንግድ ባንክ አካውንታቸው ገቢ የተደረገላቸው መሆኑ በክሱ ተጠቁሟል።
11ኛ ተከሳሽ ደግሞ በልደታ ክ/ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ውስጥ የይዞታ ማህደር ባለሙያ በመሆን በምታገለግልበት ጊዜ በ10ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ከንፋስ ስልክ ላፍቶ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ለልደታ ክ/ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት ”የላክናቸውን 6 ማህደሮችና ካርታ እንድትረከቡን ” በሚል ሀሰተኛ የሽኝት ደብዳቤ በነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም ይዘው የቀረቡ እና 11ኛ ተከሳሽም ማህደሮቹን ተቀብላ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ሳይሰጣት ሀሰተኛ ማህደሮች ወደ መዝገብ ቤት በራሷ ገቢ እንዲሆኑ ማድረጓ በክሱ ተመላክቷል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ከ6 ማህደሮች ውስጥ በ4ኛ እና በ8ኛ ተከሳሾች ስም የተዘጋጁት ማህደሮች የጀርባ ማህተም አገልገሎት እንዲያገኙ በመደረጉ እና ሁለት ይዞታዎችን በ 18 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በሽያጭ ለሌላ 3ኛ ወገን እንዲተላለፉ በማድረግ ሒደት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን በመንግስት እና ግለሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ስልጣንን ያለአግበብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሳለች።
በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ በአጠቃላይ በመንግስት ላይ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱ በክሱ ላይ ተመላክቷል።
ተረኛ ችሎቱ በችሎት ለቀረቡ ሁለት ተከሳሾች ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ከተከላካይ ጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡ እንዲሁም በሌላ ወንጀል ተከሰው ማረሚያ ቤት ያሉ ተከሳሾች በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ አዝዟል፡፡
ችሎቱ ክሱን ለመመልከትም ለመስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ