Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ እና ኢራን እስረኞችን ተለዋወጡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ኢራን የእስርኛ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

ሀገራቱ አምስት አምስት እስረኞችን የተለዋወጡ ሲሆን፥ አሜሪካ የታገደ የኢራንን 6 ቢሊየን ዶላር በተጨማሪነት መልቀቋም ነው የተሰማው።

የእስረኛ ልውውጡ በዋሺንግተን እና ቴህራን መካከል ለወራት የዘለቀው ድርድር ውጤት መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ፥ አምስቱ አሜሪካውያን ከቴህራን በትናንትናው ዕለት ተነስተው ከኳታር ወደ ዋሺንግተን አምርተዋል።

ከእስር የተለቀቁት አሜሪካውያን በቴህራን በስለላ ወንጀል ተከሰው የአሥር ዓመት እስራት የተፈረደባቸው መሆናቸውን አር ቲ አስነብቧል።

የኢራኑ ኑር ኒውስ ጋዜጣ በአሜሪካ በቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ኢራናውያን በተመሳሳይ ጊዜ መለቀቃቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ከመካከላቸው ሁለቱ ሰኞ ዕለት ኳታር ገብተው ወደ ኢራን የሚጓዙ ሲሆን፥ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ ለመቆየት መምረጣቸውን ነው ዘገባው ያመላከተው።

የኢራን ማዕከላዊ ባንክ ገዥ መሃመድሬዛ ፋርዚን የቴህራን የነዳጅ ሽያጭ ገንዘብ የሆነውና ታግዶ የነበረው 6 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ በኢራን ባንኮች ገቢ መደረጉ ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ሪፐብሊካኖች ደግሞ ዋሺንግተን ገንዘቡን መልቀቋ ቴህራን ወደፊት ተጨማሪ አሜሪካውያንን እንድትይዝ ያበረታታታል በሚል ወቀሳ አቅርበዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የተለቀቀው ገንዘብ አጠቃቀም ላይ ገደብ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ኢራን የተለቀቀውን ገንዘብ እንደ ምግብ እና መድኃኒት ለመሳሰሉት ሰብዓዊ አቅርቦቶች ብቻ እንድታውል ይደረጋል ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ፥ “ቴህራን ገንዘቡን እንዳሻት ትጠቀምበታለች” ሲሉ መናገራቸውም ነው የተሰማው፡፡

አሜሪካ በፈረንጆቹ 2015 ከተደረሰው የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ከወጣች በኋላ፥ ኢራን ከነዳጅና ሌሎች ምርቶች ሽያጭ ማግኘት የነበረባት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘቧ በዋሺንግተን ማዕቀብ ሳቢያ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ ይገኛል።

#America #Iran #exchangeprisoners

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.