የብሪቲሽ ወረቀት ማምረቻ በሩሲያ የሚገኘውን ፋብሪካ ሊሸጥ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪቲሽ የወረቀት እና የማሸጊያ አምራች ኩባንያ ‘ሞንዲ’ ሀገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ለመውጣት በሩሲያ የቀረውን የመጨረሻ ፋብሪካ ለመሸጥ ከስምምነት መድረሱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በሰጠው መግለጫ የወረቀት ማምረቻውን በሞስኮ ለሚገኘው የሪል ስቴት ገንቢ ሴዛር ግሩፕ በ80 ቢሊየን ሩብል ወይም በ825 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ለመሸጥ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጿል።
ፋብሪካው በሩሲያ ወረቀትና ካርቶን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን÷ ወደ 4 ሺህ 500 ለሚጠጉ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ 2022 መገባደጃ ላይም በጥቅሉ ወደ 1 ነጥብ 16 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንዳገኘ ተጠቁሟል።
ኩባንያው ከሩሲያ ፀረ-ሞኖፖሊ ኤጀንሲ እና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ከሚመለከተው የመንግስት ኮሚሽን ፈቃድ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን÷ ሽያጩ በታህሳስ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክቷል።
በፈረንጆቹ 2023 መጀመሪያ ላይ ሞንዲ መቀመጫቸውን በሩሲያ ያደረጉ ሦስት የማሸጊያ ማምረቻ ፋብሪካዎቹን ለጎቴክ ግሩፕ በ16 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር መሸጡን አር ቲ ዘግቧል።
ሞንዲ ከ30 በላይ ሀገሮች ውስጥ 22 ሺህ ሠራተኞች ያሉት ዓለም አቀፍ የወረቀት እና ማሸጊያ አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን÷ በፈረንጆቹ 2022 ብቻ 9 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱም ተመላክቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!