ትዊተር አገልግሎቱን በክፍያ ሊያደርግ ይችላል እየተባለ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኤክስ ምልክት ራሱን እንደ አዲስ እያስተዋወቀ የሚገኘው ትዊተር አገልግሎቱን በክፍያ ሊያደርግ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
ኤሎን መስክ ሐሳቡን የገለጸው ከእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ተገናኝተው በመከሩበት ወቅት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ኤሎን መስክን ማነጋገር የፈለጉበት አንዱ ምክንያት አይሁድ ጠል ልጥፎች በትዊተር ማኅበራዊ ትሥሥር ገፅ ላይ አለቅጥ መለቀቃቸውን ተከትሎ ከሕዝባቸው ዘንድ ተቃውሞ ስለበረታባቸው ነው፡፡
ኤሎን መስክ÷ ለአይሁድ ጠል ልጥፎቹ መበራከት ባለ አስተውሎ ሮቦቶችን ጨምሮ ማንም ግለሰብ እንደ ፈቀደ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጹን መለያ መፍጠር በመቻሉ መሆኑን በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡
ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ወርሃዊ ክፍያ ማስከፈል ነው የሚለውን ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ለሁኔታው እልባት እንደሚያበጅለት ሙሉ ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ቢሊየነሩ በእስራዔል በቴክኖሎጂ ና አርተፊሺያል አስተውሎ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ በትብብር እንዲሠራ ያላቸውን ፍላጎት ትናንት በትዊተር ማኅበራዊ ትሥሥር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አመላክተዋል፡፡