በሊቢያ የደረሰው የጎርፍ አደጋ የሀገሪቱን ምስራቃዊ ክፍል መሰረተ ልማት 70 በመቶውን እንዳወደመ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሊቢያ በቅርቡ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ 70 በመቶ የሚሆነውን የአካባቢውን መሰረተ ልማትና ተቋማት ማውደሙን የሀገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በተከሰተው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ደርናን ከሱሳ፣ አልቁባና ከሌሎች ስድስት ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ሁለት ድልድዮችን ጨምሮ 11 ድልድዮች መውደማቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
በተጨማሪም÷ የጎርፍ አደጋው በተከሰተበት አካባቢ 80 በመቶ የሚሆኑት የውኃ ቧንቧዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውንና 50 በመቶ ያህሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የኒ ሳፋቅ የተባለው የሀገሪቱ የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡
የጎርፍ አደጋውን አስመለክቶ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ ባወጣው መረጃም በጎርፍ አደጋው ቢያንስ 11ሺህ 300 ሰዎች ህይዎታቸውን ሲያጡ 40 ሺህ ነዋሪዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡