ለአምራች ኢንተርፕራይዞች 132 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የአገልግሎት ድጋፍ በጀት ተመደበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተኪና የውጪ ምንዛሬ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ የሚሰማሩ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታውቋል።
በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የዓለም ባንክ፣ የልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት እና የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)፥ የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት ለማሳደግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም በተኪና የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ ለሚሰማሩ አምራች ኢንተርፕራይዞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
ለዚህም ለሥራ ማስኬጃ፣ ለካፒታል እቃ ፋይናንስና ሌሎች አገልግሎቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ኢንተርፕራይዞች ለምርታማነት፣ ለጥራት፣ ለተወዳዳሪነት፣ ለቴክኖሎጂያዊ አቅም ግንባታና ለዘላቂ የስራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።
የልማት ባንክ ተወካይ አቶ ወረደ ቃል በበኩላቸው፥ በአምራች ኢንተርፕራይዞች የሚስተዋለውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ከዓለም ባንክ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት በ2016 በጀት ዓመት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ከዓለም ባንክ የተገኘ 132 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የአገልግሎት ድጋፍ በጀት መያዙን ጠቁመዋል።
የኢንተርፕራይዞችን የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ቸግር ለመቅረፍም ኢንተርፕራይዙ 3 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱ ተጠቁሟል።
የኤሌክትሪክ ሃይልና የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ተብሏል።
በመላኩ ገድፍ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!