በቦሌ ክፍለ ከተማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለጽንፈኛ ሀይሎች ሊተላለፉ የነበሩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎች ሊተላለፉ የነበሩ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችና ሰነዶች መያዛቸው ተጠቆመ።
ጌታሁን አስፋው ጌታሁን የተባለና በአማራ ክልል የህዝብ ሰላምና ጸጥታን ለሚያውኩ ጽንፈኛ ሀይሎች የሎጅስቲክስ አቅራቢ እንደሆነ የተጠረጠረ ግለሰብ በክፍለ ከተማው ወረዳ ሁለት ቤት ተከራይቶ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በማከማቸት ለጽንፈኛ ቡድኖቹ ለማቅረብ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በጸጥታ ሀይሎች ክትትል ሊደረስበት መቻሉ ተነግሯል።
የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ግለሰቡ ከተከራየው ቤት ወታደራዊ ቁቁሶችና ሰነድ ተይዟል።
በዚህም የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች፣ የመካከለኛና የረጅም ርቀት ወታደራዊ የመገናኛ መሳሪያዎች፣ ልዩ ልዩ ትጥቆችና ወታደራዊ አልባሳት፣ የተለያዩ ሰነዶችና ጽንፈኛ ሀይሎቹ የሚጠቀሙባቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች መያዛቸው ተገልጿል።
ከመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ውጭ በግለሰቦች እጅ ሊኖር የማይገባ የከፍተኛ ርቀት ወታደራዊ የመገናኛ መሳሪያም ከተያዙት ቁሳቁሶች መካከል እንደሚገኝበት ተጠቁሟል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም መታወቂያዎችን በማውጣት ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ከአማራ ክልል በመሰወር በአዲስ አበባ ከተማ የግለሰብ ቤት በመከራየት ለጽንፈኛ ሀይሎች ሎጅስቲክስ ሲያሰባስብና ስልጠናዎችንም ሲሰጥ መቆየቱም ነው የተገለጸው።
ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ክትትል እየተደረገና ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!