Fana: At a Speed of Life!

ሕዳሴ ግድብ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል – ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘርፈ ብዙ የልማት ተጠቃሚነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

አቶ አሻድሊ ሃሰን ÷ አራተኛና የመጨረሻ ዙር ሙሌት ተጨማሪ የሃይል ማመንጨት አቅም የሚፈጥርና ከፍተኛ ውሃ የተያዘበት በመሆኑ ለአካባቢው ትልቅ ፀጋ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከሃይል አቅርቦት ባሻገር ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ተናግረዋል።

በግድቡ ምክንያት የተፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሀይቅና ከ70 በላይ ደሴቶች ተከትሎ በርካታ የመዝናኛ ሥፍራዎች እንደሚኖሩ ጠቁመው፤ ይህም ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት።

ሰው ሰራሽ ሃይቁ ለዓሣ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ በተጨባጭ እየታየ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ፤ ይህም ለክልሉ ህዝብና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

ሕዳሴ ግድብ ይዞት የመጣው ዕድል የአካባቢው ወጣቶችንና ኢንቨስተሮችን ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚያደርግም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ግድቡ ይዞት የመጣውን የልማት ዕድል በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የክልሉን ማኅበረሰብ እድገትና የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዕቅድ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.