Fana: At a Speed of Life!

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው- ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ገለፁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማከናወን አለመቻሉን ማስታወቁን ተከትሎ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥበት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በሂደቱ ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሰብሳቢዋ ወይዘሮ መአዛ በመግለጫቸው፥ የቀረበውን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ዙሪያም አሁን ላይ በስራ ላይ ባሉ 10 የጉባኤው አባላት ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጓሜ የሚያስፈልገው መሆኑ ይመረምራል ያሉት ወይዘሮ መአዛ፥  ትርጓሜ የሚሰጠው ጥያቄም ከሆነ የውሳኔ ሀሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረባል ብለዋል።

ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮም ከህግ ባለሞያዎች ጋር ለህዝብ የሚተላለፍ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት ።

በሀይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.