Fana: At a Speed of Life!

ያለአግባብ መሬት እንዲወሰድ በማድረግ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ የሙስና ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለስድስት ግለሰቦች ያለአግባብ 1 ሺህ 700 ካሬ ሜትር ይዞታ እንዲወስዱ በማድረግ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉ 21 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ተረኛ ችሎት ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ የተከሳሾችን የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ አጠቃላይ 21 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 1ኛ ተከሳሽ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ክ የብልጽግና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የቀድሞ የወረዳ 1 አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አብዮት ባገዘ ኤርጋንዶ፣ 2ኛ ተከሳሽ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ክ አረንጓዴ ልማት እና ተፋሰስ ጽ/ቤት ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ይዲዲያ ከበደ ሙሉነህ ፣ 3ኛ ተከሳሽ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ክ የህግ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ ሰለሞን ደሳለኝ ፣ 4ኛ ተከሳሽ በክ/ከተማው የመደበኛ ይዞታ ማስቀጠል የስራ ሂደት መሪ ዮሳን ሁንዴን ጨምሮ 14 የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች እና ሰባት በግል ስራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ይገኙበታል።

1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ እስከ 15 ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱ ተከሳሾች ጋር  በመሆን በወረዳ 1 በስራ አስፈጻሚነት ሲሰራ መመሪያዎቹን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት ሲገባው ኃላፊነቱን ወደጎን በመተው ስልጣኑን አለአግባብ በመገልገል በወረዳው በአርሶአደርነት የማይታወቁ የነዋሪነት ሰነድ የሌላቸውን ስድስት  ተከሳሾች በልማት ተነሺነት ይስተናገዱ የሚል ማረጋገጫ በመስጠትና ነባር አርሶ አደሮች ከሆኑት የዐቃቤ ህግ ሶስት ምስክር ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ቀላቅሎ የልማት ተነሺ ናቸው በማለት በነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ደብዳቤ መላኩን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

2ኛ ተከሳሽ ደግሞ 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር የሆኑትን ግለሰብ ” መንግስት ለድሃ ድሃ የቤት መስሪያ ቦታ እየሰጠ ስለሆነ ቦታው እንዲሰጥሽ አስደርጋለሁ” በማለት መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም ግለሰቧ ለራሱ የውክልና ስልጣን እንድትሰጠው ካደረገ በኋላ ፎቶግራፍ ፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ ያላገባ የምስክር ወረቀት ያስፈልጋል በማለት ከምስክሯ  በመቀበል በምስክሯ ስም የልማት ተነሺነት ጥያቄ በማቅረብ የውክልና ስልጣኑን ተጠቅሞ በድጋሚ ለ15ኛ ተከሳሽ ውክልና መስጠቱ በክሱ ዝርዝር ተጠቅሷል።

15ኛ ተከሳሽ ደግሞ ውክልናውን ከ2ኛ ተከሳሽ በተቀበለ ማግስት የ500 ካሬ ሜትር የምትክ ይዞታን ተረክቦ ለሌላ ወገን በ4 ሚሊየን 500 ሺህ ብር መሸጡ በክሱ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል 1ኛ ተከሳሽ  ከ16ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር 16ኛ ተከሳሽ ነባር አርሶ አደር ከሆኑት ግለሰብ ላይ ሚያዚያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የመኖሪያ ቤት ግዢ እንደፈጸመች በማስመሰል፥ የቤት ሽያጭ የመንደር ውልን በመጠቀም የልማት ተነሺ እንደሆነችና በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ክ ወረዳ 1 ውስጥ በአርሶ አደርነት የግብርና ስራ እየሰራች  የምትኖርበት በማስመሰል  ምትክ ቦታውን እንድትወስድ እና በወኪሏ አማካኝነት ቦታው እንዲሸጥ መደረጉን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክሱ አመላክቷል።

በዚህ መልኩ በተለያዩ ቀናት ለስድስት ግለሰቦች በተለያዩ መጠኖች በየደረጃው አጠቃላይ 1 ሺህ 700 ካሬ ሜትር ይዞታ የልማት ተነሺ አርሶ አደርነት ምትክ ቦታ እንዲወስዱ መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹ  በሰነድ አጣሪነት፣ በመረጃ አሰባሰብ፣ በይዞታ አረጋገጭና አጽዳቂነት፣ የቅድመ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በማዘጋጀትና መብት በመፍጠር እንዲሁም ያለአግባብ ይዞታ ተረክቦ በመሸጥ ረገድ እንደ ስራ ድርሻቸው ተሳትፏቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ ለልማት ተነሺዎች ሊሰጥ የሚገባውን ቦታ በህገ ወጥ መንገድ እንዲወሰድ በማድረግ እና ወስዶ በመሸጥ በመንግስት ላይም የሊዝ ዋጋው 30 ሚሊየን 640 ሺህ 84 ብር ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራነት እና በልዩ የሙስና ወንጀል ተካፋይነት ስልጣንን አለአግባብ መገልገል የከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛው ክስ ደግሞ  2ኛ ፣ 16ኛ እና 21ኛ ተከሳሾች 500 ካሬ ሜትር በ15ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ከተሸጠ 4 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ውስጥ  የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ተከፋፍለው ተጠቅመዋል ተብለው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በመስጠት ለመስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.