Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም መስህቦች ልማት ባሻገር ዘርፉን የማዘመን ስራ መከናወኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም መስህቦች ልማት ባሻገር ቱሪዝምን ለማሳደግ ዘርፉን የማዘመን ስራዎች መሰራታቸውን የክልሎ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የዘንድሮውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንትና የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በመግለጫቸው÷ በክልሉ የቱሪዝም እሳቤን የማሳደግ፣ ዘርፉን የማዘመን፣ ሀብቶችንና መዳረሻዎችን የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የማስተዋወቅና ማነቃቃት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት 9 ነጥብ 5 ሚሊየን የሀገር ውስጥና 235 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ማስተናገድ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2016 ዓ.ም የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ገልጸው፤ በመርሐ-ግብሩ የኦሮሚያን ይጎብኙ ብራንድ ማስተዋወቅ፣ የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ የቁንጅና ውድድር፣ የቱሪዝም ኤግዚቢሽንና ሌሎች ኹነቶች እንደሚካሄዱ አመላክተዋል፡፡

የሰላምና የይቅርታ በዓል የሆነው ኢሬቻም የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ የሚከበር በዓል መሆኑን ገልጸው፤ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በዓሉን በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ተገኝተው የሚታደሙ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቷ ቱሪዝም እድገት የጎላ ሚና እንዳለው አቶ ነጋ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.