በሪጋ 2023 የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በላቲቪያ ሪጋ በሚካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በጎዳና ውድድሩ አምስት የዓለም ሪከርድ የሰበሩ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን÷ የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን አትሌቶችን ጨምሮ 347 አትሌቶች በስድስት ርቀቶች ይሳተፋሉ፡፡
ከመስከረም 20 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በሶስት ርቀቶች በ19 አትሌቶች እንደምትወከል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በሪጋ የአንድ ማይል የጎዳና ውድድር ኢትዮጵያውያኖቹ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ሃይሉ በውድድሩ የማሸነፍ ቅደመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚሁ ርቀት የ5 ሺህ ሜትር ባለ ሪከርዷ ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዮገን እና አውስተራሊያዊቷ አትሌት ጄሲካ ሃል ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በ5 ኪሎ ሜትር በሚደረገው ውድድር በሴቶች አትሌት መዲና ኢሳ፣ ለምለም ሃይሉ እና እጅጋየሁ ታዬ ሲሳተፋ÷ በወንዶች በሪሁ አረጋዊ ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሀጎስ ገብረ ሕይወት ኢትዮጵያን ይወክላሉ።
በሌላ በኩል በወንዶች ግማሽ ማራቶን ጀማል ይመር ፣ ንብረት መላክ ፣ ድንቃለም አየለና ፀጋዬ ኪዳኑ ኢትዮጵያን ሲወክሉ÷ በሴቶች ደግሞ መስታወት ፍቅር፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እና ፍታው ዘራይ ይሳተፋሉ ።