Fana: At a Speed of Life!

ለግጭቶች እልባት በመስጠት ሰላምን እናጽና – የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግጭት ምክንያቶችን ለይቶ በማውጣት እልባት በመስጠትና ሰላምን በማጽናት በኩል ሁሉም ዜጋ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በአጀንደ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመምረጥ በጋምቤላ ከተማ ለሦስት ቀናት ያካሄደው መድረክ ተጠናቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፈን አርዓያ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያለምንም ግጭት በሰላምና በአንድነት የኖሩባት ሀገር ናት፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመግባባቶች እየሰፉ ግጭቶች የተከሰቱበት ሁኔታ መስተዋሉንም ነው ያነሱት።

ባለመግባባት ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረትና ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ህዝቦች ችግር ሲገጥም በመነጋገርና በመመካከር ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

በተለይም መሰረታዊ የግጭት መንስዔ የሆኑ ምክንያቶችን ለይቶ በጋራ መፍታት ከተቻለ ሁሉም የሰላም አሸናፊ እንደሚሆንም ነው ያስረዱት።

ግቡን ለማሳካት በሁሉም አካባቢዎች ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት በአጀንዳ ልየታ መድረክ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችን ኮሚሽኑ እያስመረጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ከጋምቤላ ክልል ከሚገኙ 13 ወረዳዎችና ከጋምቤላ ከተማ መስተዳድር በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ 504 ተወካዮችን እንዳስመረጠ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.