Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ዙርያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይፈጠር እየሰሩ መሆኑን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙርያ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በግብፅ ያረጀ አስተሳሰብ ቅስቀሳ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይፈጠርበት ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን በአሜሪካ እና እንግሊዝ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ተናገሩ።

የምጣኔ ሀብት እና የግጭት አፈታት ተመራማሪ የሁኑት ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ እና ዶክተር ልዑልሰገድ አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በኢንተርኔት ባደረጉት ውይይት የግብፅ ፔንዱለማዊ ዥዋዥዌ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በአሜሪካ ከ50 ዓመታት በላይ የሰሩት አሁንም በምዕራብ ኤልኖዌይ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ፥ ከሰሞኑ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በዓባይ ጉዳይ ላይ ስለ ኢትዮጵያ አካሄድ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በተለያዩ የጥናት መፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ ፅሁፋቸውን አሳትመዋል።

ፕሮፌሰር ተሾመ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታም፥ የግብፆች አካሄድ በዛሬ መስታዋት ብቻ የተገደበ አይደለም ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እንዳታመጣ በድህነት አረንቋ እንድትማቅቅ የዓባይ ፖለቲካን መሰረት ያደረገ ሴራ መከወናቸውንም ይናገራሉ።

የግጭት አፈታት ተመራማሪ እና ኗሪነታቸውን እንግሊዝ ለንደን ያደረጉት ዶክተር ልዑልሰገድ አበበ በበኩላቸው፥ የዓባይ ውሃ የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ላይ ያዘነበለ ሆኖ አይቀጥልም፤ ዓባይ የሁላችንም ነው ሲሉ ከለንደን ባሰራጩት ሰፋያለ ትንታኔ ለአለም አቀፉ ማህብረሰብ ግልፅነት፣ ለግብፆችም ራሳቸውን እንዲያዩ እንዲሁም ለካርቱሞቹም አካሄዳቸውን ቆም ብለው እንዲያጤኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር ልዑልሰገድ አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታም፥ ማነኛውም ሀገር በተፈጥሮ ሀብቱ የመጠቀም መብት አለው ይላሉ።

የካይሮ ሰዎች የሄድ መለስ የውሃ ፖለቲካ አካሄድ መነሻው ኢትዮጵያዊያኖች ተባብረው ለምን ዓባይን ደፈሩት ቁጭት እና ንፉግነት ነው ብለዋል።

ዶክተር ልዑልሰገድ በህዳሴው ግድብ ዙርያ ኢትዮጵያ እየተከተለቸው ያለው አካሄድ የሚያስመሰግናት ነበር ይላሉ።

በስላባት ማናዬ

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.