Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ 500 ሺህ ለሚደርሱ የቬኒዝዌላ ፍልሰተኞች የሥራ ፈቃድ ሰጠች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከፈረንጆቹ ነኀሤ ወር በፊት ድንበር አቋርጠው ለገቡ 500 ሺህ ያኅል የቬኒዝዌላ ፍልሰተኞች የሥራ ፈቃድ ሰጠች፡፡

የባይደን አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በበርካታ የቬኒዝዌላ ጥገኝነት ጠያቂዎች በመጨናነቁ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡

ውሳኔው ከአንድ ወር ወዲህ የቀረቡትን ጥያቄዎች አይመለከትም ተብሏል፡፡

አሁን ላይ በኒውዮርክ ከሚታዩት ፍልሰተኞች መካከል 40 በመቶዎቹ ቬኒዝዌላውያን ናቸው፡፡

በኒውዮርክ ኅግ መሠረት ለፍልሰተኞች ቢያንስ መጠለያ ማቅረብ ግድ ስለሚል በየወሩ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ መጠጊያ ፈላጊዎች ወደ ውዷ የንግድ ከተማ ያቀናሉ ተብሏል፡፡

ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 12 ቢሊየን ዶላር ያኅል በጀት ያስፈልገኛል በሚል አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ለገባው የከተማዋ አስተዳደር በሀገር ደረጃ በባይደን አስተዳደር የተሰጠው ውሳኔ እፎይታን ሰጥቷል፡፡

የኒውዮርክ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ለውሳኔው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ያመሰገኑ ሲሆን ከዚህ በኋላ የስደተኞች ጉዳይ የኒውዮርክ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ከተሞች አስተዳደር እና የአሜሪካ ነው ብለዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዚህ በኋላ ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገሪቷ መግባት የሚሞክሩትን ፍልሰተኞች ለመቆጣጠር የሚውል 4 ቢሊየን ዶላር የደኅንነት ጥበቃ እና ፍልሰት ቅነሳ በጀት እንዲጸድቅላቸው ለኮንግረሳቸው አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.