ኢትዮጵያና አሜሪካ የ230 ሚሊየን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያና አሜሪካ መንግስት የ230 ሚሊየን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።
የልማት ትብብር ስምምነቱን አሜሪካ በዓለም አቀፉ የዩናይትድ ስቴት ልማት ተርአዶ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በኩል ከኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ጋር መፈራረሟን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመላክቷል።
የ230 ሚሊየን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነቱንም የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ተርደኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴያን ጆንስ ፈርመዋል።
ስምምነቱ አሜሪካ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ እድገት እና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል የምታደርግውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑም ታውቋል።
በአዲሱ የልማት ትብብር ስምምነት ማእቀፍ ውስጥም የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ተርደኦ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ከሌሎች ዓለም አቀፍ እና ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመሆን የጤና ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እንዲሁም በግል ዘርፍ የሚመራ ሞዴል የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የሚሰራ መሆኑም ታውቋል።
ዩ.ኤስ.ኤይድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴያን ጆንስ በፊርማው ወቅት፥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አጋርነታችንን የሚያድስ ስምምነት በመፈራረማችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
አዲስ የተፈረመው ስምምነት ከገንዘብ በላይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት የዘለቀውን የህዝብ ለህዝብ አጋርነት የሚያጠናክር እና በጋራ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚረዳ ነው ብለዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።