በአፋር የቱሪዝም ሃብትን በማልማትና በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ያለውን የቱሪዝም ሀብት በማልማትና በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የዓለም ቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሃብቶችና ባህሎችን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራም ተመላክቷል።
በቢሮው የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዱ አህመድ እንደገለጹት÷ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን በአግባቡ በማልማት ክልሉንና ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በክልሉ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ከመለየት ጀምሮ የይዞታ ካርታ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ባለሃብቶች በሆቴሎች እና ሎጂዎች ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
በክልሉ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኀላፊ አቶ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው በ2016 ዓ.ም በቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራትን ለማጠናከር እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን መከበሩ ሊጠፉ የተቃረቡ ባህሎች እንደገና እንዲያንሰራሩና ያሉ የቱሪዝም ሃብቶችን ለማስተዋወቅ የራሱ አስተዋጾ እንዳለውም ነው የገለጹት።