ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን በ54ኛው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያቀረበውን ሪፖርት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው አስታውቃለች።
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ በሰጡት ማብራሪያ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የማትቀበለው እንደሆነ ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ኢትዮጵያ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥረቷን አጠናክራ እንደቀጠለች ተናግረዋል።
የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የሚያስችል የሰላም አማራጭ መንገድን በመከተል የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በኩል በርካታ ጥረት ቢደረግም ቡድኑ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የተካሄደውን የሰላም ማስፈን ሂደትን ጨምሮ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለመቀበል ፍላጎት አለማሳየቱን አስረድተዋል።
እጅግ በጣም አጠያያቂ በሆኑ የአሰራር ዘዴዎችና በጣም ራቅ ካሉ አካባቢዎች በተገኘ መረጃ መሰረት የተጠናቀረው የቡድኑ ሪፖርትና ግኝቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አወንታዊ የፖለቲካ እድገቶች በእጅጉ ያዛባ ነው ብለዋል።
ሪፖርቱ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጥምረት የተካሄደውን የምርመራ ውጤትም የተቃረነ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
መንግስት ለመተባበር ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ቡድኑ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ፖለቲካዊ ግምገማ ለማድረግ መምረጡንም ነው ያመለከቱት።
ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን መስፈርቶች የሚያሟሉ ማስረጃዎችን ቡድኑ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልፀው፤ ሪፖርቱ በአብዛኛው ወገንተኛ አስተያየቶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነም አብራርተዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ አሉታዊና በአብዛኛው ያልተረጋገጡ አስተያየቶችን ቡድኑ ማስተጋባቱን አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ጋባዥነት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ማሰማራታቸውን ገልፀዋል።
በዚህ ስምሪት የተገኘው ማንኛውም ግኝት በመንግስት በኩል የእርምትና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚጠቅምም አስገንዝበዋል።