ኢስተርን ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ ቤቶችን መገንባት እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ኢስተርን ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ቤቶችን ለመገንባትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የትራንስፎርሜሽንና ዋና ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም ከተማ ከኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቪድ ሃም እና ልዑካቸው ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ፍፁም÷ ኢስተርን ኮርፖሬሽን በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት ለማድረግና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ያሳየውን ከፍተኛ ፍላጎት አድንቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመርና የሰራተኛውን ምቹ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያግዙ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኩባንያው ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
የኢስተርን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቪድ ሃም በበኩላቸው÷ ኩባንያቸው በአሜሪካ በተለያዩ ግንባታዎች ላይ ያካበተውን ልምድ በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ማቀዱን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በዘርፉ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት እንዳለው ነው የገለጹት፡፡
ኢስተርን ኩባንያ በአሜሪካ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከ25 ዓመታት በላይ በቤቶች ግንባታ እንዲሁም በፕሮጀክት ማስተዳደር ዘርፍ የካበተ ልምድ ያለው መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡