ጁሌያን ኔግልስማን የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የባየርሙኒክ አሰልጣኝ ጁሊያን ኔግልስማን በአንድ ዓመት ኮንትራት የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ተሹመዋል፡፡
የ36 ዓመቱ አሰልጣኝ በቅርቡ የተሰናበቱትን የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በመተካት ነው ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት፡፡
ከስምምነቱ በኋላ ኔግልስማን በቀጣዩ ክረምት በጀርመን በሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
“ከፊትችን የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ አለ፣ከብዙ ዓመታት በበኋላ በሚዘጋጀው መድረክ ከቡደኑ ጋር በመዋሃድ ውጤታማ ለመሆን እንሰራለን” ብለዋል፡፡
ስኬታማ ከሚባሉት ወጣት አሰልጣኞች የሚመደቡት ጁሊያን ኔግልስማን÷በጀርመኑ ሆፈኒየም የአሰልጣኝነት ስራቸውን የጀመሩ ሲሆን አርቢ ሌብዚሽ እና ባየርሙኒክን ማሰልጠናቸው የሚታወስ ነው፡፡
ወጣቱ አሰልጣኝ በአርቢ ሌብዚሽ ቆይታቸው ክለቡን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለግማሽ ፍፃሜ ማድረስ የቻሉ ሲሆን÷ በባየርሙኒክ ቆይታቸው ደግሞ የቡንደስሊጋ ዋንጫን እና ሁለት የጀርመን ሱፐርካፕ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል፡፡