“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የወጣ እንጂ የተጫነ ዕዳ አይደለም”- ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማይተካውን የሰዎች ሕይወት ለመታደግ የወጣ እንጂ በዜጎች ለይ የተጫነ ዕዳ አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቋቋመውና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከመርማሪ ቦርዱ አባላት ጋር በአዋጁ አፈጻጸም ላይ ዛሬ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ ወረርሽኙን መቆጣጠር አዳጋች ይሆናል።
በቫይረሱ ዙሪያ ዜጎች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲከላከሉ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በበርካቶች ዘንድ መዘናጋት እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “የማይተካውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ የወጣ እንጂ በዜጎች ላይ የተጫና ዕዳ አይደለም” ብለዋል።
በመሆኑም ለአዋጁ ተፈጻሚነት እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን መወጣት አንዳለበት አሳስበዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ለኮሚቴው በሰጠው የአንድ ወር አፈጻጸም ግብረ መልስ ሰጥቷል።
በዚህም ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በማስፈጸም ረገድ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በበጎ ጎን አንስቷል።
የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ቦርዱ ከደረሱት አቤቱታዎች ከ80 በመቶ በላይ መንግሥት መመሪያውን እያስፈጸመ አለመሆኑን ገልጸው፤ ይህም የግንዛቤ ማስጨበጡ ሥራን ማስቀደም የተሻለ አማራጭ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በተለይም መመሪያውን ከማስፈጸም አኳያ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አለመኖራቸውን አንስተዋል።
በትራንስፖርትና በገበያ ሥፍራዎች አሁንም መመሪያውን የመጣስ አዝማሚያዎች እየታዩ በመሆኑ በአፋጣኝ እንዲስተካከል ቦርዱ ጠይቋል።
በድንበር አካባቢ የማቆያ ሥፍራዎች በበቂ ሁኔታ እንዲሟሉና በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ዜጎች ላይም ክትትሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።