በዓላቱ ያለፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል – የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት አከባበር ያለፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ገልፀዋል።
የኢሬቻ በዓልን በተመለከተም ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሸገር ከተማ ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፥ በእነዚህ የአደባባይ በዓላት አከባበር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የወንጀል እና የፀጥታ ስጋቶችን ለማስወገድ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የተለያዩ አጋዥ ኃይሎችም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እስከ ብሎክ በማደራጀት እና በማስተሳሰር ወደ ተግባር ተገብቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በውይይቱ ላይ እንዳነሱት፥ በዓላቱን የማይመለከቱ እና የሌሎችን መብት እና ነፃነት የሚጋፉ ሐሳቦችን በጽሑፍም ሆነ በሌሎች ዓርማ እና ምልክቶች ማንፀባረቅ ክልክል በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ለፀጥታው ሥራ ሲባል በዓሉ በከተማ ደረጃ በሚከበርበት ስፍራ ፍተሻ ስለሚኖር የበዓሉ ታዳሚዎች ለፀጥታ አካላቱ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ኮሚሽነር ጌቱ አስረድተዋል።
በዓለቱ በሚከበሩበት ወቅት ምንም አይነት ርችት መተኮስ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ግብረ ኃይሉ አሳስቦ ይህንን በመተላለፍ ርችት ሲተኩስ የተገኘ ግለሰብም ሆነ ተቋም ላይ በህግ አግባብ እርምጃ የሚውስድ መሆኑን አስታውቋል።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የቅድመ መከላከል ሥራውን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን በመረዳት ኅብረተሰቡ እስካሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኅብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አስተላልፏል።