አልቡርሃን ለሰላም ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ለሰላም ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።
አል ቡርሃን ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጋር ለሰላም ድርድር ለመቀመጥ ፈቃደኛ ነኝ ብለዋል።
በኒውዮርኩ 78ኛ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅም አሁን ላይ ለሰላም ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ለንጹሃን ዜጎች ከለላ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አሁን ካለበትና ንጹሃን ከሚገኙበት መኖሪያ አካባቢ ሃይሉን ካስወጣና ወደ ነበረበት ከተመለሰ ከዚህ በፊት በተደረሰው መሰረት ለሰላም ድርድር መቀመጥ እንችላለንም ነው ያሉት አልቡርሃን።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ ሐምዳን ዳጋሎም በዚህ ሳምንት በተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልዕክት ለሰላም ድርድር ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።
ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለው የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን እልባት ያላገኘ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም የተደረሱ የሰላም ስምምነቶችም በተደጋጋሚ ተጥሰዋል።
በሱዳን ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን ተመድ አስታውቋል።