የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር ውይይት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ልዑካን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ውይይቱ እየተካሄደ ያለው በፈረንጆቹ 2015 በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ መሰረት በስኬት ከተከናወነው አራተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዚህ ዙር ውይይት ሀገራቱ በጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አያይዘውም በመርሆዎች መግለጫው በተቀመጠው መሰረት በአባይ ውሃ አጠቃቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ማስፈን ብቸኛው አማራጭ መሆኑን መግለፃቸውን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም ሒደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቁርጠኝነት የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት አረጋግጠዋል።
የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሐኒ ሴዊላም (ፕ/ር) እና የሱዳን ተጠባባቂ የውሃ ሚኒስትር ዳውልበይት አብድልረህማን ማንሱር ባሽር÷ በመክፈቻ ንግግሮቻቸው በድርድሩ ሒደት ከስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ፅኑ ተስፋ ገልጸዋል።