በቤኒን የነዳጅ ማከማቻ በደረሰ የእሳት አደጋ የ35 ሰዎች ሕይዎት አለፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒን የነዳጅ ማከማቻ መጋዘን ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 35 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡
አደጋው ቤኒን ከናይጄሪያ ጋር በምትዋሰንበር ድንበር ላይ በምትገኘው ሴሜ-ፖድጂ ከተማ በሚገኝ ሕገ ወጥ የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
በዚህም አደጋው አንድ ህጻንን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይዎት የነጠቀ ሲሆን የንግድ ሱቆችንና የተለያዩ ንብረቶችን ማውደሙን የሀገሪቱ የሥራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡
አደጋው በተከሰተበት ወቅት መኪናዎች፣ ሞተር ብስክሌቶችና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ለመቅዳት መገኘታቸውም ነው የተጠቀሰው፡፡
የቤኒን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አላሳኔ ሲዱ እንዳሉት፥ የአደጋው ምክንያት ነዳጅን በሕገወጥ መልኩ ማከማቸት ነው፡፡
አልጀዚራ በዘገባው ቤኒን ከናይጄሪያ በምትዋሰነው ድንበር አካባቢ ሕገወጥ የነዳጅ ዝውውሩ የተለመደ እንደሆነ አንስቶ፥ ይሕም በሕገወጥ የነዳጅ ማከማቻ ቦታዎች የእሳት አደጋ እያስከተለ ነው ብሏል፡፡
የሀገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለውም፥ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው፡፡