Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ የጉራጌ ባሕላዊ እሴቶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉራጌ ባሕላዊ እሴቶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር÷ የጉራጌ ዞን በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሮሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች መገኛ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዞኑ የጉራጌ ክትፎ አዘገጃጀት፣ ባሕላዊ የቤት አሰራር፣ የጉራጌ የመንደር (ጀፎረ) አሰራር፣ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት (ቂጫ) እና ሌሎች እሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ዞንም እነዚህ የጉራጌ ባህላዊ እሴቶችን በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ለባለስልጣኑ ጥያቄ ማቅረቡን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንም ጥያቄውን ተቀብሎ ባህላዊ እሴቶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው÷ መስቀል ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ጉራጌ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል አድርጎ እንደሚያከብረው አስረድተዋል።

ማህበረሰቡ በበዓሉ ወቅት የተጣላ ካለ እርቅ የሚፈጽምበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት፣ ወላጆች ልጆቻቸው የሚመርቁበት፣ ደስታቸው የሚገልጹበትና ሌሎች መልካም ተግባራት የሚከውኑበት ነው ብለዋል።

የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሔር የመቻቻል፣ የአብሮነትና ማንነቱን የሚገለጽበት በመሆኑ ትውልዱ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መናገራቸውንም የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.