ፈረንሳይ ዲፕሎማቶቿን እና ወታደሮቿን ከኒጀር እንደምታስወጣ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ-መንግስት ተከትሎ ፈረንሳይ ዲፕሎማቶቿን እና ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ገለጸች።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ÷ ሀገራቸው በኒጀር ያሏትን አምባሳደሮች እና በርካታ ዲፕሎማቶች በሠዓታት ዕድሜ ውስጥ ለማስወጣት መወሰኗን እንደተናገሩ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ማክሮን ከኒጀር ጋር የነበራቸውንም ወታደራዊ ትብብር ‘አብቅቷል’ ያሉ ሲሆን ኃይላቸውን እስከ መጪዎቹ ወራት አስወጥተው እንደሚጨርሱ ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ ሐምሌ ወር በመፈንቅለ-መንግሥት ኃይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል የፈረንሳይን ውሳኔ በደስታ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ማክሮን በመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከሥልጣን ለተባረሩት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙም እውቅና እንደሚሰጡም ነው የገለጹት።
ከኒጀር መንግስት ጋር በነበረው የትብብር ማዕቀፍ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር 1 ሺህ 500 የሚጠጉ የፈረንሳይ ወታደሮች አሉ፡፡
የአሁኑ ውሳኔ ፈረንሳይ ከኒጀር ለቃ እንድትወጣ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ለወራት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ የመጣ መሆኑም ታውቋል።