Fana: At a Speed of Life!

በነዳጅ የበለጸጉ ሀገራት የዓየር ንብረት ታክስ መክፈል አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነዳጅ የበለጸጉ ሀገራት አዳጊ ሀገራት የዓየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንዲረዳቸው ታክስ መክፈል አለባቸው ሲሉ የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ገለፁ።

ጎርደን ብራውን እንዳሉት እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ ኳታር እና ኖርዌይ ያሉ ሀገራት ባለፈው ዓመት የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ትርፋማ ናቸው፡፡

በዚህም የ25 ቢሊየን ዶላር ቀረጥ ለአዳጊ ሀገራት የዓየር ንብረት ፈንድ ስምምነት ሊደረግ ይገባል ማለታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።

በኒውዮርክ በተካሄደው የተመድ የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ የዓለም መሪዎች የካርበን ልቀትን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ ነው ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ከፍተኛ የካርበን ልቀት የሚያደርጉ ሀገራት’ በዓየር ንብረት ትብብር ላይ እንዲስማሙና የካርበን ልቀትን ለመቀነስና ለአዳጊ ሀገራት ድጋፍ እንዲያደርጉም ነው የጠየቁት፡፡

ጎርደን ብራውን በበኩላቸው ነዳጅ ላኪ ሀገራት በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት “ሊገመት የማይችል ትርፍ” አስመዝግበዋል ነው ያሉት።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር የነበረው የዓለም የነዳጅና የጋዝ ገቢ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ 4 ትሪሊየን ዶላር ከፍ ማለቱንም ነው ያነሱት፡፡

ይሕም ከዓለም አቀፍ የእርዳታ በጀት 20 እጥፍ የሚበልጥ መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል።

“ይሕ ከፍተኛ ትርፍ ከአዳጊ ሀገራት ጉሮሮ የተነጠቀ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

አክለውም የነዳጅ እና ጋዝ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በዓለም ዙሪያ ተጨማሪ 141 ሚሊየን ሰዎችን ወደ አስከፊ ድህነት መክትተቱንም አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.