Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ማዋል የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የቀጠናው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም ተናገሩ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ÷ እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ቀጠናው አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ቀደም ሲል የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበረው ወደ ነፃ የንግድ ቀጠና ከተለወጠ ወዲህ በቀጠናው መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ለማዋል የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።

በቀጠናው የተገነቡ 15 ሼዶች በሙሉ በውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በአሁኑ ወቅት ተይዘው መጠናቀቃቸው ነፃ የንግድ ቀጠናው ያመጣው ውጤት መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ካሚል እንዳሉት ለሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የሚጠበቀው የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ባለፈው ዓመት ከ10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል።

ከውጭ ሀገራት በምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በንግድ ቀጠናው በማምረት የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደተቻለ ጠቁመው÷ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የነፃ ንግድ ቀጠናውን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባትና ለልማት የሚኖረውን አበርክቶ ዕውን ለማድረግ የሚያስችል የነፃ ንግድ ቀጠናዎች አዋጅ ዘንድሮ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

አዋጁ በቀጠናው ሼድ የወሰዱ ባለሀብቶች በሙሉ አቅም ወደሥራ ለማስገባት የነበሩ የህግና የአሠራር ከፍተቶችን ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ነፃ የንግድ ቀጠናው አሁን እየሰጠ ካለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተጨማሪ የሎጂስቲክ እና የንግድ ዘርፎችን ወደሥራ በማስገባት ልማቱን ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.