የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ1 ሺህ 335 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 335 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በክልሉ 8 ማረሚያ ቤቶች በተለያዩ ፍ/ቤቶች ውሳኔ አግኝተው የፍርድ ጊዜያቸውን በመፈፀም ላይ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም 1 ሺህ 329 ታራሚዎች መደበኛ ሙሉ ይቅርታ ያገኙ ሲሆን÷ 6 ታራሚዎች ደግሞ የእስራት ቅናሽ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል።
ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል 79ኙ ሴቶች እንደሆኑ መግለጻቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑት ታራሚዎች ከፍርድ ጊዜያቸው 1/2ኛ እና 1/3ኛውን ያሟሉ እና ስለመታረማቸውና መታነፃቸው ማረጋገጫ የተሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡