ባንኩ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2016 በጀት ዓመት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ዕቅድ መያዙን አስታወቀ።
የባንኩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የአብሥራ ከበደ÷ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ ባንኩ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በእውቀትና ክህሎት የሚመሩ ጠንካራ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ ተከታታይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት አራት ዙር ሥልጠናዎችም 133 ሺህ ዜጎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
ሥልጠናውን ለመውሰድ ተመዝግበው ከሚጠባበቁ 320 ሺህ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መካከል በበጀት ዓመቱ እስከ 75 በመቶ ያህሉን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አብራርተዋል።
ሥልጠና የወሰዱ የብድር አገልግሎት ፈላጊ ዜጎችም የገበያ አዋጭነት ሃሳባቸውን ለባንኩ ማቅረብ እንዳለባቸው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ባንኩ ብድር በመስጠት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ አንቀሳቃሾች 20 ከመቶ የስራ ማሟላት ያለባቸው ሲሆን÷ ባንኩ የቴክኒክና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ 80 ከመቶ ብድር እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል።
እስካሁን ስልጠናውን ተከታትለው የንግድ እቅዳቸውን ላቀረቡ ዜጎች 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ባንኩ መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
በ2016 በጀት ዓመትም የባንኩን ስልጥና በአግባቡ ለተከታተሉና ዝርዝር የንግድ ስራ እቅድ ለሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች 20 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።
የባንኩ የፋይናነስ አካታችነትን ለማረጋገጥ አማራጮችን እያሰፋ መሆኑን ገልጸው፤ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ዜጎች የብድር አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።