በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ ፊጦናአላመስኖ ቀበሌ አራጌቻ በተባለ ስፍራ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
አደጋው ዛሬ ከረፋዱ 5:30 አካባቢ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን ሲጓዝ የነበረ አነስተኛ ህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ከሚጓዝ ተሳቢ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ የደረሰ ነው ተብሏል፡፡
በአደጋው በአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሶስት ወንድና የአንድ ሴት ተሳፋሪ ህይወት ሲያልፍ በርካታ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን አምሳሉ በሪሁን ተናረዋል፡፡
የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረው በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ለህክምና ወደሸኖ እና ደብረብርሃን ሆስፒታሎች መወሰዳቸው ገልፀዋል፡፡
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በታለ ማሞ