በቱሪዝም ሴክተሩ ትልልቅ ውጤት ያመጡ ሥራዎች ተሰርተዋል- አቶ ሽመልስ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንደ ክልልና እንደ አገር ትልልቅ ውጤት ያመጡ ሥራዎችን መፈጸም መቻሉን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ”ቱሪዝም ሳምንት” አውድ ርዕይን የጎበኙ ሲሆን ይህን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷በጉብኝታቸው በሴክተሩ የበለጠ ለመስራት ያሚያነሳሱና የሴክተሩን ባለድርሻ አካላት ሊያነቃቁ የሚችሉ ተግባራትን መመልከታቸውን አስፍረዋል፡፡
ይህም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት፣ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) በተመዘገበ ማግሥት በመሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል፡፡
መንግስት የቱሪዝም ሴክተር በክልሉና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት እንዲችል ሴክተሩን የሚመጥን አወቃቀር በመገንባትና በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።
በዚህም የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሠጠውን ትልቅ ተልዕኮ ወስዶ ወደ ሥራ በገባ ሦስት የምሥረታ ዓመታት ውስጥ ብቻ እንደ ክልልና እንደ ሀገር ትልልቅ ውጤት ያመጡ ሥራዎችን ከመፈጸም አልፎ እንደ ምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ትልቅ መነቃቃት መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ አውድ ርዕይ ትልቅ ተስፋ የሚያጎናፅፉ ሥራዎችን ማየታቸውንና በሌላ በኩል ሴክተሩ የሚያመነጨው የሥራ ዕድል- የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የባሕል እቃዎች አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ የሆቴልና የመዝናኛ አገልግሎት አቅርቦት ከመሳሰሉት ተጠቃሚ ለመሆን በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የ3ኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡