የመስቀል በዓል የአብሮነትና የተስፋ ተምሳሌት ነው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል በዓል የአብሮነት፣ የትጋት፣ የጽናት፣ የትእግሥትና የተስፋ ተምሳሌት ነው ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ለ2016 ዓ.ም ለደመራና መስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንደ ደመራ ችቦ ኅብር ፈጥረው ኢትዮጵያን እውን አድርገዋል ብለዋል፡፡
ችቦዎቹ ኅብር ፈጥረው እንዲቆሙ የሚያስችሉት አምዶችም ሀገር በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቆም ከሚያደርጉ የጋራ እሴቶቻችን ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፡፡
ተደምረን በአብሮነት ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ ከተነሳን እንደ ደመራው ብርሃን ከፍ ብለንና ደምቀን እንታያለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የመስቀል በዓልን ስናከብርም ከአፍራሽ ተግባራት በመራቅ በመደጋገፍና በመመካከር ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለጋራ ዕድገት በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡