Fana: At a Speed of Life!

ርዕሳነ-መስተዳድሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ- መስተዳድሮች ለደመራ እና ነገ ለሚከበረው የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት÷ መስቀል የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እንዲሁም የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት እሴታችን ደምቆ የሚታይበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር የሃይማኖቱ አስተምህሮ የሆኑትን አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ ፍቅርና መከባበርን በማስፈን ረገድ ለሁሉም አርአያ ሆኖ በመገኘት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት÷ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የፍቅር፣ የእርቅ እና የይቅርታ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በክልሉ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል መስቀል አንዱ መሆኑን በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የመተባበር፣ የአብሮነት እና የእርስ በርስ መደጋገፍ እሴቶች በጉልህ የሚንፀባረቁበትና ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረ የመጣ እንደሆነ አመልክተዋል።

እንዲሁም የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሕብረተሰቡ የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባሕሉን በመተግበር በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።

የተጀመረው የእድገት ጉዞ እውን እንዲሆን በየአካባቢያችን ሰላማችንን አጽንተን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ሙሉ አቅማችንንና ትኩረታችንን በልማት ላይ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.