Fana: At a Speed of Life!

የመስቀልን በዓል ስናከብር የእምነቱን አስተምህሮ በማሰብ ሊሆን ይገባል – ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደመራና መስቀል በዓል ሲከበር የክርስትና ሃይማኖትን አስተምኅሮ በማሰብና እርስ በርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ የክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች ገለጹ፡፡

የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች ለ2016 ዓ.ም የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ደመራና መስቀል የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላት በኩል ፋይዳቸው የላቀ ነው ብለዋል።

በዓሉ የተስፋ፣ የልምላሜና እንደገና በአዲስ መንፈስ ለስራ የምንነሳሳበት ነው በማለት ገልጸው፤ በዓሉን ስናከብርም የሃይማኖቱ አስተምኅሮ የሆኑትን አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ መከባበርንና ሠላምን በማስተማርና አረአያ ሆኖ በመገኘት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

እንዲሁም የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ባስላለፈው መልዕክት ሕዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር÷ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እንዲሁም የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባሕሉን በመተግበር ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል፡፡

የክልሉ ሕዝብም ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርን፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት በክልሉ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የልማት ተግባራት እንዲያጠናክር ጥሪ አቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በዓሉ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታና መተሳሰብ የሚገለፅበት መሆኑን ገልጸው÷ በዓሉ የኢትዮጵያዊነት ማድመቂያ የእርስ በርስ መዋደድ መገለጫ ሊሆን እንደሚገባ በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

ከሃይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር የቱሪዝም ሀብት የሆነውን የመስቀል በዓል÷ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዓሉን በፍቅር፣ በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ማክበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው÷ በበዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንደ ደመራው ሁሉ እንደ አንድ በመደመር በጽናት በማለፍ ከፊት ያለውን ተስፋ መጠበቅ እንደሚገባ አስገንበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.