የቦንጋና ኡሊያኖቭስክ የፔዳጎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር ለመሥራት መከሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሩሲያው ኡሊያኖቭስክ የፔዳጎጂ ዩኒቨርሲቲ በትብብር መሥራት በሚችሉበት ማዕቀፍ ላይ መከሩ፡፡
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) በሞስኮ የሚገኘውን የሩሲያ ትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡
በቆይታቸውም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በትብብር መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)÷ ከኡሊያኖቭስክ የፔዳጎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢጎር ፔትቼቭና ከፓን አፍሪካ የሕዝብ አጋርነት ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኦክሳና ማዮሮቫ (ፕሮፌሰር) ጋር በመሆን የሩሲያን የትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሰርጌይ ማሊሼቭን አግኝተዋቸዋል፡፡
የኡሊያኖቭስክ የፔዳጎጂ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ በግብርና እና ጤና ዘርፍ የትምህርትና የምርምር ሥራዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ቃል ገብቷል።
የፓን አፍሪካ የሕዝብ አጋርነት ልማት ማዕከል በበኩሉ÷ በኢትዮጵያ በቡና ምርትና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎችና ኢንተርፕራይዞች ሥልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቡና፣ ሙዝ እና በሌሎች ፍራፍሬዎች ላይ የሚያሰለጥን ማዕከል በአዲስ አበባ ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁንም አመላክቷል፡፡
40 የሚደርሱ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ውይይቱን በበይነ መረብ መከታተላቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም በቡና ምርምር ላይ ማዕከል አቋቁሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ለዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በቀጣይም በማስተርስ እና በዶክትሬት ዲግሪም ሥልጠናዎችን የመሥጠት ዕቅድ አለው።
በወንደሰን አረጋኸኝ