የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊ እሴቶች ለመጠበቅ ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ እንደሚደረግ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ለመጠበቅና ለማልማት ለሚከናወኑ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ አስታወቁ፡፡
አቶ ቀጄላ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከናወነው የመስቀል ደመራ ሥነ- ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የመስቀል በዓል ፍቅር፣ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ አንድነትና ሰላምን የሚያስተምር መሆኑን አንስተዋል፡፡
የበዓሉን አስተምኅሮ በመከተል በሰላም አብረን ልንኖር ይገባናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በትዕግስት፣ በንግግርና በይቅርታ በማለፍ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
መንግሥት የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠበቁና እንዲለሙ እንዲሁም ለትውልድ እንዲተላለፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡