ኢትዮጵያዊው በዱባይ ዱቲ ፍሪ ሎተሪ አንድ ሚሊየን ዶላር አሸነፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ነዋሪነቱ በዱባይ የሆነው ኢትዮጵያዊው ተክሊት ተስፋዬ በዱባይ ዱቲ ፍሪ ሎተሪ የአንድ ሚሊየን ዶላር አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ።
ከተክሊት ተስፋዬ ጋር አንድ ህንዳዊ በተመሳሳይ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ዕጣ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል።
የዱባይ ዱቲ ፍሪ ሎተሪ ከጀመረበት ከፈረንጆቹ 1999 አንስቶ ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሲሆኑ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ተገልጿል።
በዚህ በአሁኑ ዕጣ ከተክሊት ጋር የዕጣው አሸናፊ የሆነው የዱባይ ነዋሪ ህንዳዊው ሻምሱዲን ቼሩቫታንታቪዳ ነው።
ከገንዘብ አሸናፊዎቹ በተጨማሪ ሶስት ዕድለኞች ቅንጡ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን አሸንፈዋል።
የሻርጃህ ነዋሪ ህንዳዊት ሳማይራ ግሮቨር ከሙምባይ ወደ ዱባይ ስትበር በገዛችው ትኬት ቢኤምደብሊዩ መኪና ለማሸነፍ በቅታለች።
የዱባይ ዱቲ ፍሪ ሎተሪ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም ዋዜማ ጀምሮ ‘ሚሊኒየም ሚሊየነር’ በሚል ርዕስ የሚካሄድ የሎተሪ ጨዋታ ሲሆን የአንድ ዕጣ ዋጋ 1 ሺህ ድርሃም (278 ዶላር) ነው።