የአማራ ክልልን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚባ ተገለፀ።
በባህር ዳር ከተማ ከሚገኙ የክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በግሽ ዓባይና ዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተሞች በተደረገው ህዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት ስነ- ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል ሽፈራው ቢሊሶ ÷ የሠራዊቱ ድርሻ የህዝቡንና የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ በመሆኑ በዚህ አግባብ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በአፄ ቴዎድሮስና በጣና ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ዳዊት እንዳለ በበኩላቸው ÷ የክልሉን ሠላም ወደ ቀደመው ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም ገልፀዋል።
አክለውም ፥ ከህዝብ አብራክ ወጥቶ ህዝባዊ ተልዕኮን በመወጣት ላይ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ስምና ዝናን ለማጠልሸት ፅንፈኞች የሚነዙትን አሉባልታ ህብረተሰቡ ሊኮንነው ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
በውይይት ላይ የተመሰረተ አማራጭን መከተል እንደሚገባና ህዝቡ የራሱን ሚና መለየትና መወጣት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ያለ መከላከያ ሠራዊቱ ሀገር ሠላሟ ሊጠበቅና ህዝቡ ህልውናው ሊረጋገጥ ስለማይችል የሰራዊቱን ስምና ዝና የሚያጠለሹ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ፤ መንግስትም የህብረተሰቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ይመልሳል ብለዋል።
ህዝባዊ ውይይቱ በባህርዳር ከተማ ከሚገኙ ከሁሉም ክፍለከተማ ነዋሪዎች ጋር የተደረገ ሲሆን ÷ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተገልጿል።